Saturday, July 30, 2011

ቅዳስ ያሬድ

ቅዳስ ያሬድ አባቱ አብድዩ /ይስሐቅ/ እናቱ ክርስቲና /ታውክልያ/ ይባላሉ /በሌላም በኩል አባቱ እንበረም እናቱ ትውልያ ይባላሉ የሚል ታሪክም አለ፡፡/ የትውልድ ሥፍራው አከሱም ነው፡፡ የተወለደው በ505 ዓ.ም/ ሚያዝያ 5 ቀን የሚል አለ/ ሲሆን በተወለደ በ7 ዓመቱ ወላጅ አባቱ ስለሞተ እናቱ የአክሱም ጽዮን መምህር ለነበረው ለአጎቱ ለጌዴዎን እያስተማረ እንዲያሳድገው ሰጠችው፡፡ ከአባ ጌዴዎንም ዘንድ እየተማረ ለ25 ዓመት ተቀመጠ፡፡

ሆኖም ቃለ እግዚአብሔር የመቀበል ችሎታው ደካማ ስለሆነ በጣም ያዝን ነበር፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን ከትምህርት ድክመቱ የተነሣ አጎቱ በጨንገር ቢገርፈው በዚህ ተበሳጭቶ ትምህርቱን ትቶ ሄደ፡፡ በመንገድም ሲጓዝ ውሎ በቀትር ደክሞት ከዛፍ ሥር ዐረፈ፡፡ በዚያ ጊዜ አንድ ትል ከዛፉ ላይ ያለውን ፍሬ ለመብላት ስድስት ጊዜ በመውደቅና በመነሣት ዛፉ ላይ ለመውጣት ሞክሮ በሰባተኛው ሰተት ብሎ ወጥቶ ሲበላ ተመለከተ፡፡ እርሱም በፈጸመው የብስጭት ተግባር በመጸጸት ተመልሶና አጎቱን ይቅርታ ጠይቆ ትምህርቱን ቀጠለ፡፡ አጎቱም ተደስቶ ዓይነ ልቡናውን ያበራለት ዘንድ እያለቀሰ ፈጣሪውን ለመነለት፡፡ እግዚአብሔርም ጸሎቱን ሰምቶ ለቅዱስ ያሬድ ዕውቀትን ገልጾለት መጻሕፍተ ብሉያትንና ሐዲሳትን ዐወቀ፡፡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ይህን በተመለከተ

ሰላም ለያሬድ ስብሐተ መላእክት ለሕዋጼ
እንተ አዕረገ በልቡ ኅሊና መንፈስ ረዋጼ
ለትምህርተ መጽሐፍ ገብአ እምኀበ ኮነ ነፋጼ
በብዙኀ ፃማ ዘአልቦ ሐጻጼ
መልዕልተ ዕፅ /ኮሞ/ ነጸሮ እንዘ የዐርግ ዕጼ

የሚል ዐርኬ ደርሰውለታል፡፡ ይህን አርኬ የድጓ መምህራን ጠዋት ጉባኤ ሲዘረጉ ተማሪዎቻቸውን ያስደርሷቸዋል፡፡

ከዚያም በኋላ ወደ መምህሩ ተመልሶ ትምህርቱን ቀጠለና ቅዱሳት መጻሕፍትን በሚገባ አጠና፡፡ ሢመተ ዲቁናን ቀጥሎም ሢመተ ቅስናን ተቀበለ፡፡ ቅዱስ ያሬድ ግእዝ፣ እዝልና አራራይን ከሦስት ወፎች/መላእክት በወፎች ተመስለው/ መማሩን ሊቃውንት ይገልጣሉ፡፡ እነዚህ በወፍ የተመሰሉ መላእክት እየመሩት ወደ አርአያም አርጎ የ24ቱን ካህናተ ሰማይ ዜማ ከተማረ በኋላ ጠዋት በ3 ሰዓት በአክሱም ቤተ ክርስቲያን «ሃሌ ሉያ ለአብ ሃሌ ሉያ ለወልድ ሃሌ ሉያ ለመንፈስ ቅዱስ ቀዳሚሃ ለጽዮን ሣረረ ወበዳግመ አረአዮ ለሙሴ ዘከመ ይግበር ግብራ ለደብተራ» ብሎ አዜመ፡፡ ይህን ዜማ የደረሰበት ወሩ ታኅሳስ ቀኑም ዕለተ ሰኞ ነው ይባላል፡፡ የቅዱስ ያሬድ የመጀመሪያ ዜማው «አርያም» በመባል ይታወቃል፡፡ ይህም ከመላእክት ወይም ከሰማይ የተገኘ መሆኑን ለማጠየቅ የተሰጠው ስም ነው፡፡

ቅዱስ ያሬድ ይህንን ዜማ በተመስጦ ሲያዜም ንጉሡ፣ንግሥቲቱ፣ ጳጳሱ መኳንንቱና ካህናቱ ወደ አኩስም ቤተ ክርስቲያን ተሰባስበው መጥተው በአድናቆት ያዳምጡት ነበር፡፡ ምክንያቱም ገደለ ቅዱስ ያሬድ እንደሚገልጥልን ከዚያ በፊት በውርድ ንባብ ከሚደረግ ጸሎትና መንፈሳዊ አገልገሎት በቀር ይህን የመሰለ ዜማ አልነበረምና፡፡

የቅዱስ ያሬድ ድርሰት ብሉይን ከሐዲስ ያስማማ፣የሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንን ትምህርት በሚገባ የያዘ፣ እንዲሁም ለልዑል እግዚአብሔር፣ለእመቤታችን፣ለቅዱሳን መላእክት፣ ለጻድቃንና ለሰማዕታት ተገቢ የሆነውን ምስጋና የያዘ ነው፡፡ ከዚህም በላይ ለአራቱ የዓመቱ ወቅቶች እንዲስማማ አድርጎ ለበጋ፣ ለክረምት፣ ለመጸውና ለጸደይ እንደሚሆን አድርጎ ከፋፍሏቸዋል፡፡ ለየበዓላቱም ተስማሚ ድርሰት መድቦላቸዋል፡፡ ይህንን ድርሰቱን በግእዝ፣ በእዝልና በአራራይ ዜማ ያዘጋጀው ሲሆን ለነዚህም ስምንት የዜማ ምልክቶች ሠርቶላቸዋል፡፡

የቅዱስ ያሬድ ዜማ አንዴት ሁሉንም ይመስጥና ወደ አርያም በመንፈስ ይወስድ እንደ ነበር ለማስረዳት በገድሉም በሌሎችም መጻሕፍት የተመዘገቡ ታሪኮች አሉ፡፡ አንድ ቀን ንጉሥ ገብረ መስቀል፣ንግሥቲቱ፣ ጳጳሱ፣ ካህናቱና ምእመናኑ በተሰባሰቡበት ቅዱስ ያሬድ ዜማውን ሲያዜም ንጉሡ በመመሰጡ የተነሣ በመሰቀል ተሰላጢኑ ጫፍ የቅዱስ ያሬድን እግር ወጋው፡፡ ነገር ግን ማንም አላወቀም ነበር፡፡ ቅዱስ ያሬድ መዝሙሩን ሲፈጽም ንጉሡ መስቀል ተሰላጢኑን ቢያነሳው የቅዱስ ያሬድ ደሙ ፈሰሰ፡፡ ንጉሡ በዚህ ደንግጦ ለዚህ ካሣ ይሆን ዘንድ የፈለግከውን ጠይቀኝ እሰጥሃለሁ ብሎ ቃል ገባለት፡፡ ቅዱስ ያሬድ ግን ከዚህ ዓለም ተለይቶ በምናኔ መኖርና መዝሙሩንም በሚገባ ማዘጋጀት እንደሚፈልግ ገለጠ፡፡ ምንም እንኳን አኩስምን ለቅቆ መውጣቱ ንጉሡን ቅር ቢያሰኘውም ቃሉን አንድ ጊዜ በመስጠቱ ምንም ሊያደርገው አልቻለም፡፡ ቅዱስ ያሬድም ከዚህ በኋላ አኩስምን ለቅቆ ወደ ስሜን ተራራ ጸለምት መጓዙ ይነገራል፡፡

በጐንደር ፎገራ በሚባል ሥፍራ ቅዱስ ያሬድ ጣዕም ያለው ዜማውን ሲዘምር ተጠምደው የሚያርሱ በሬዎች ድምፁን እየሰሙ ገበሬውን ሥራ ስለ አስፈቱት በዚህ ተናዶ ቅዱስ ያሬድን በጅራፍ እንደ ገረፈው ይነገራል፡፡ ቦታውም «ወርቀ ደም´ እየተባለ እስከ ዛሬ ይጠራል፡፡ ወርቃማና ንጹሕ ደሙ የፈሰሰበት ማለት ነው፡፡

ቅዱስ ያሬድ ዜማውን ያዘጋጀበት ዘመን ከ540-560 ዓ.ም. ባለው ጊዜ መሆኑ ይነገራል፡፡ ዜማውን ካዘጋጀ በኋላ 11 ዓመት አስተምሯል፡፡ በእርሱ ዘመን ተሰዓቱ ቅዱሳን በሃይማኖት ችግር ምክንያት ወደ ኢትዮጵያ ተሰደው መጥተው ስለ ነበር ቅዱስ ያሬድ ከአንዱ ከአባ ጰንጠሌዎን የውጭውን ሀገር ቤተ ክርስቲያን ባሕልና ሥርዓት ይጠይቅ ነበር፡፡ በጆሮ የሰማውንም በዓይን ለማየት ሁለት ጊዜ ሮም የተባለችውን የቁስጥንጥንያ ቤተ ክርስቲያን ጐበኘሁ ይላል፡፡ «ወሪድየ ብሔረ ሮሜ ለቤተ ክርስቲያን ርዒክዋ» እንዲል፡፡ የታሪክ ምሁሩ ሥርግው ሀብለ ሥላሴ ለቁስጥንጥንያ ዜማ መነሻው ቅዱስ ያሬድ ነው ይላሉ፡፡ ለዚህም ማስረጃ የሚያደርጉት የቁስጥንጥንያን ዜማ የደረሰው ሊቅ ዜማውን አገኘው የሚባለው የቅድስት ሶፍያን ቤተ ክርስቲያን ሲዞር ከሰማው ዜማ ነው፡፡ ይህ ዘመን ደግሞ ቅዱስ ያሬድ ከተነሣበትና ወደ ሮሜ ሄድኩ ካለበት ዘመን ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ እናም ምናልባት ያ ሰው ዜማውን የሰማው የቅድስት ሶፍያ ቤተ ክርስቲያንን እየዞረ ሲዘምር ከነበረው ከቅዱስ ያሬድ ሳይሆን አይቀርም ይላሉ፡፡ Ancient and medival Ethiopian History/

ቅዱስ ያሬድ ማትያስና ዮሴፍ በተባሉ የአቡነ አረጋዊ ደቀ መዛሙርት መሪነት ወደ ደብረ ዳሞ ተራራ ላይ ወጥቶ ከጻድቁ ጋር በመገናኘትና የቤተ ክርስቲያኑን ሥራ እያደነቀ ዙሪያውን ከዞረ በኋላ «ዖድክዋ ወርኢኩ ሥነ ሕንፃሃ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን» ሲል ዘመረ፡፡ በዚያም ለአንድ ሳምንት ሰንብቶ ሄዷል፡፡

ቅዱስ ያሬደ ከአቡነ አረጋዊ እና ከዐፄ ገብረ መስቀል ጋር በመሆን በወሎ፣ በጎንደር፣ በሸዋ እና እስከ ጋሞጎፋ ብርብር ማርያም ድረስ በመሄድ አስተምሯል፡፡ አንዳንድ መረጃዎች የዐርባ ምንጭን ታሪክ ከቅዱስ ያሬድ፣ ከአቡነ አረጋዊ እና ከዐፄ ገብረ መስቀል ታሪክ ጋር ያያይዙታል፡፡ ሦስቱም ብርብር ማርያምን ለማየት ሄደው በነበረ ጊዜ በዛሬው ዐርባ ምንሥ አካባቢ ሠፍረው ነበር፡፡ በዚያ ቦታ ለወታደሩ የሚበቃ የሚጠጣ ውኃ በመጥፋቱ አቡነ አረጋዊ ጸልየው መሬቱን በመስቀል ቢመቱት ዐርባ ውኃዎች ፈለቁ ይባላል፡፡

ዐፄ ገብረ መስቀል የጣና ቂርቆስን ቤተ ክርስቲያንን በሚያሠራ ጊዜ በዚያ ቦታ ለሁለት ዓመት ተቀምጦ ድጓውን በማስተማሩ ምልክት የሌለው ድጓው እስከ ዛሬ በገዳሙ ይገኛል፡፡ ቀጥሎም የዙር አባን ቤተ ክርስቲያን ለማሠራት ወደ ጋይንት በተጓዙ ጊዜም በዚያ ሁለት ዓመት ዝማሬ መዋሥዕት የተባለ ድርሰቱን አስተምሯል፡፡ ይህ ቦታ እስከ ዛሬ የዚህ ትምህርት ማስመስከሪያ ነው፡፡

ቅዱስ ያሬድ ከዚያ በኋላ ወደ አከሱም ተመልሶ በመደባይ ታብር በተባለ ቦታ ቅዳሴያትን በዜማ አዘጋጅቷል፡፡ ይህ ቦታ ከአከሱም 15 ኪ.ሜትር ርቆ ይገኛል፡፡ ከዚህ በኋላ ለመጨረሻ ጊዜ አኩስምን ተሰናብቶ ለመሄድ ወደ ጽዮን ቤተ ክርስቲያን ገባና «ቅድስት ወብጽዕት ስብሕት ወቡርክት ክብርት ወልዕልት አንቀጸ ብርሃን ማዕርገ ሕይወት» እያለ አንቀጸ ብርሃን የተባለውን ድርሰቱን ሰተት አድርጎ አዘጋጀው፡፡ ይህንን ድርሰት ሲያዜም አንድ ክንድ ያህል ከምድር ከፍ ብሎ ይታይ ነበር ይባላል፡፡

ቅዱስ ያሬድ በሰሜንና ወገራ፣ አገውና በጌምድር እየተዘዋወረ አስተምሮ ከሰሜን ተራራዎች ውስጥ እየጾመና እየ[ለየ በብሕትውና ለብዙ ዘመን ከኖረ በኋላ በሰሜናዊ ምሥራቅ በኩል ባለው በጸለምት ዋሻ ውስጥ በ571 ዓ.ም ግንቦት 11 ቀን ተሠውሯል፡፡ ይህ ቦታ በተለምዶ የሰሜን ተራሮች በሚባለው ወስጥ የሚገኝ ከፍተኛና ብርዳማ ቦታ ነው፡፡

ቅዱስ ያሬድ ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሰማያዊ ዜማን ከማበርከቱም ሌላ በትምህርት ሂደትም አስተዋጽዖ አድርጓል፡፡ የድጓን፣ የጾመ ድጓን የዝማሬ መዋሥዕትንና የቅዳሴን ትምህርት ከማስተማሩም በላይ ለቅኔ ትምህርትም መሠረት ጥሏል፡፡

Saturday, July 2, 2011

ዘማሪ እስጢፋኖስ ሳህሌ

ዘማሪ እስጢፋኖስ ሳህሌ ከአርሂቡ መጽሔት ጋር ስለ ተሃድሶ ምንነት እና በቤተ ክርስቲያን ላይ እየደረሰ ያለውን አደጋ አስመልክቶ ያደረገውን ቃለ ምልልስ እና ስለ እሱም አገልግሎት ከተጠርጣሪዎች (ተሃድሶ ናቸው) ከሚባሉት ግለሰቦች ጋር የነበረውን ቆይታ ምን እንደሚመስል እና ተሃድሶ ማለት ምን ማለት እንደሆነ በቃለ መጠይቁ ውስጥ ያገኙታል መልካም ንባባ (ምንጭ ደጀ ሰላም)

Monday, June 27, 2011

ዘማሪ እስጢፋኖስ ሣህሌ (ቄሴ) ምእመኑን ይቅርታ እየጠየቀ ነው




  • Read this News in PDF.
  • “እኛ የአባቶችን አገልግሎት ለማስረሳት ሠራን፤ የእነርሱም ኀዘን እኛን ጣለን፡፡›› (እስጢፋኖስ ሣህሌ)
  • በተለያዩ አህጉረ ስብከት ሕገ ወጥ ሰባክያንንና እና ዘማርያንን የመከላከሉ ጥረት ተጠናክሮ ቀጥሏል፤
  • በጋሻው ደሳለኝ “በቪሲዲ የተሰራጨብኝ ማስረጃ በአኒሜሽን የተቀናበረ ነው!!›› አለ
  • በቅዱስ ሚካኤል ክብረ በዓል ዋዜማ በሜጋ - ሞያሌ መንገድ የመኪና አደጋ የደረሰባቸው ምርትነሽ ጥላሁን እና አሰግድ ሣህሉ በሕክምና ላይ ናቸው
(ደጀ ሰላም፤ ጁን 24/2011)፦ በደብረ አሚን ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን አጥቢያ ወጣቶች ግንቦት 27 ቀን 2003 ዓ.ም የአካላዊ ቅጣት ርምጃ ከተወሰደባቸው መካከል አንዱ የነበረው ዘማሪ እስጢፋኖስ ሣህሌ (በቅጽል ስሙ ቄሴ) የሕገ ወጥ ‹ሰባክያን› እና ‹ዘማርያን› አካል እና አባል በመሆን ባደረጋቸው እንቅስቃሴዎች የተጸጸተ መሆኑን በመግለጽ ካህናት እና ምእመናን ይቅርታ እንዲያደርጉለት እየጠየቀ ነው፡፡ “እኔ ከእነርሱ የተለየሁት ከአንድ ዓመት ከመንፈቅ በፊት ነው፤በዘማሪ ፈቃዱ አማረ የጋብቻ ሥነ ሥርዐት ዕለት ወጣቶቹ የወሰዱት ርምጃ ስለ ቅንዐተ ቤተ ክርስቲያን የፈጸሙት እንጂ በግል ጥላቻ ወይም በስሜታዊነት ተነሣስተው አለመሆኑን አምኜበታለሁ” ያለው ዘማሪ እስጢፋኖስ ከሕገ ወጥ ቡድኑ ጋራ ለረጅም ጊዜ አብሮ ስለቆየበት ሁኔታ ለቀረበለት ጥያቄ ሲመልስ “ከዛሬ  ነገ የተሻለ ነገር አያለሁ በሚል ተስፋ በማድረግ ነበር”ብሏል፡፡

ዘማሪ እስጢፋኖስ ሕገ ወጥ ‹ሰባክያኑ› እና ‹ዘማርያኑ› ዐውደ ምሕረቱን የሣቅ ቀን/መድረክ ሲያስመስሉ፣ ካህናቱን እና መሪጌቶቹን በስድብ ሲያሸማቅቁ፣ ራስን ባለመግዛት የተለያዩ አስነዋሪ ድርጊቶችን ሲፈጽሙ በግልጽ ይቃወማቸው እንደ ነበር ለማስረዳት በመሞከር ላይ ይገኛል፡፡ ከሁሉም ነገር በላይ ለሰዓታቱ፣ ለማሕሌቱ እና ለቅዳሴው እንዳይተጋ “ባዶ ቤተ ክርስቲያን ሄደህ ምን ታደርጋለህ?›› እያሉ ያደረሱበት ጫና፣ ይሄዱባቸው በነበሩ አጥቢያዎች በአብዛኞቹ ካህናቱ እና መዘምራኑ የእነርሱን ሽሙጥና ዘለፋ በመሸሽ በመንደር ርቀው ይቆዩ የነበሩበት ሁኔታ በእጅጉ እንደሚያሳዝነው ተናግሯል - ዘማሪ እስጢፋኖስ፡፡ መሠረተ እምነትን በማፋለስ፣ ሥርዐተ ቤተ ክርስቲያንን በመጣስ በሚፈጽሙት ድርጊት መቼም ተባብሯቸው እንደማያውቅ ያስረዳው ዘማሪው፣ “በየዋህነት፣ በትምህርት ማነስ ምክንያት እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ አብሬያቸው በመቆየቴ በፈጸምሁት ስሕተት ቤተ ክርስቲያኔን አሳዝኛለሁ፤ በውስጣቸው ብቆይም በአቋም መለየቴን ገልጬ ማሳየት ነበረብኝ” ብሏል፡፡

“ተሐድሶ የለም›› እያሉ በዐውደ ምሕረት ለማስተባበል የሚሞክሩትን የሕገ ቡድኑን አባላት የተቃወመው ዘማሪ እስጢፋኖስ፣ “የእነርሱ ዋነኛ ዓላማ የአባቶችን አገልግሎት ማስረሳት ነው፤ እኛ የአባቶችን አገልግሎት ለማስረሳት ሠራን፤ የእነርሱም ኀዘን እኛን ጣለን”በማለት የተሰማውን ቁጭት ገልጧል፡፡ የይቅርታ ጥያቄውን ለብዙኀን መገናኛዎች በሚሰጣቸው ቃለ ምልልሶችና በተለያዩ አጋጣሚዎች እያቀረበ የሚገኘው ዘማሪ እስጢፋኖስ ከጥቃቱ ወዲህ በተለይም አገልግሎቱ ሙሉ በሙሉ የተቋረጠ መሆኑን በመግለጽ ወደ አገልግሎቱ ተመልሶ ለበደሉ መካስ እንደሚሻ ተናግሯል፡፡

በደብረ መዊዕ ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል እና በደብረ ገሊላ ቅዱስ ዐማኑኤል ሰበካዎች ባሉ ካህናት እና ምእመናን ዘንድ የሚታወቀው ዘማሪ እስጢፋኖስ ሦስት ካሴቶች ለብቻው፣ አምስት ደግሞ በጋራ የሠራቸው የ”መዝሙራት›› ሥራዎች አሉት፡፡ “ቄሴ” የሚለውን ቅጽል ስም ያገኘው በልጅነት ዕድሜው በአምሳለ ካህን ጠምጥሞ ጠበል በመርጨቱ፣ በክብረ በዓላት በአጥቢያ አብያተ ክርስቲያን እየዞረ በመዘመሩ መሆኑን በቅርብ የሚያውቁት ይናገራሉ፡፡ በማለዳው ባጣቸው ወላጆቹ ምትክ የሁለቱ አጥቢያ ምእመናን አባትም እናትም ሆነው ያሳደጉት ዘማሪ እስጢፋኖስ ወደ ገዳማት በሚደረጉ ጉዞዎች ላይ በጨረታ በሚሰበሰቡ የርዳታ ማስተባበር ተግባራት የተመሰገነ ስጦታ እንዳለው ብዙዎች ይመሰክሩለታል፡፡ “ለአገልግሎት መሰሰት አይታይበትም፤ ልግመኝነትን አያውቅም›› የሚሉት የቅርብ ወዳጆቹ በሐመረ ኖኅ ማኅበር በኩል ለቅዱስ ፊልጶስ ቤተ ክርስቲያን/አዲስ አበባ/፣ በማኅበረ አቡነ አሮን መንክራዊ አማካይነት ለአቡነ አሮን ገዳም በተደረገው የርዳታ ማሰባሰብ ሥራ ያደረገውን ተሳትፎ ያስታውሳሉ፡፡

 
በተያያዘ ዜና የቅ/ሚካኤልን በዓል ለማክበር በሜጋ - ሞያሌ መንገድ ላይ በመጓዝ ላይ የነበሩት ምርትነሽ ጥላሁን እና አሰግድ ሣህሉ የመኪና አደጋ ደረሰባቸው በኋላ አሁን በሕክምና ላይ መሆናቸው ሲታወቅ ወዲያው ወደ ያቤሎ ሆስፒታል ተወሰድው ርዳታ እንደተደረገላቸው ተገልጿል። ቀጥሎም በሐዋሳ ሆስፒታል የታከሙ ሲሆን ምርትነሽ አዲስ አበባ በሚገኘው በቅ/ገብርኤል ሆስፒታል ተጨማሪ ሕክምና እንደተሰጣት ምንጮቻችን አብራርተዋል።

በሌላ በኩል በጋሻው ደሳለኝ በበኩሉ በተለያዩ ሚዲያዎች እየወጡ ያሉ የስሕተት ትምርቶቹን እርሱ እንዳልተናገራቸው ይልቁንም እርሱ እንደተናገራቸው ተደርጎ “በአኒሜሽን” መቀናበራቸውን ለማስተባበል በመሞከር ላይ ነው።

Thursday, June 9, 2011

የተሃድሶ ስራ በአዋሳ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን

ሕገ ወጥ ሰባክያንና ዘማርያን በደብረ አሚን ተ/ሃይማኖት የከረረ ተቃውሞ ገጠማቸው፤ የተጎሸሙም አሉ


To Read, Print and Share this Message, click HERE (PDF). ይህንን መልእክት በPDFለማንበብ፣ ለማተም እና ለሌሎች ለማዳረስ ይህንን ይጫኑ።
  • የደብረ አሚን ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን ምክሐ ደናግል ሰንበት ት/ቤት ወጣቶች በአሸናፊ ገብረ ማርያም፣ ዳግማዊ ደርቤ፣ እስጢፋኖስ ሣህሌ፣ ምርትነሽ ጥላሁን እና ሌሎች መሰሎቻቸው ላይ የአካላዊ ቅጣት ርምጃ በመውሰድ ከቅጽረ ቤተ ክርስቲያን አባረሩ፤ ከተባረሩት ውስጥ የሕገ ወጦቹን ሥራ በማተም እና በማከፋፈል ተባባሪ የሆኑ ‹‹መዝሙር ቤት›› ባለቤቶች ይገኙባቸዋል፤ ወላዋይ አገልጋዮችም አቋማቸውን እንዲያስተካክሉ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል ተብሏል
  • ወጣቶቹ ሕገ ወጦቹን የቀጡበት አኳኋን ጉዳዩ የሚመለከተው የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ከፍተኛ አስተዳደር ሕገ ወጦቹን በተጨባጭ ለመቆጣጠር ባለመቻሉ የምእመኑ ትዕግሥት እየተሟጠጠ መሆኑን እንደሚያመለክት ተገልጧል
  • ‹‹የቤተ ክርስቲያን አባቶች ዝም በማለታቸው ይህን ርምጃ ለመውሰድ ተገደናል፤ የተክለ ሃይማኖት ድል በዮሴፍም ይደገማል፤ ሕገ ወጦቹን ከአዲስ አበባ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ዐውደ ምሕረት በማጽዳት የሐዋሳን ምእመናን እምባ እናብሳለን፤ ሃይማኖታችንን መጠበቅ ብቻ ማእከል ያደረገው ርምጃችን ሕገ ወጦቹ ስሕተታቸውን አርመው የበደሉትን ምእመን ይፋዊ ይቅርታ እስኪጠይቁ አልያም ለይቶላቸው ወደ መናፍቃኑ ጎራ እስኪገቡ ድረስ ይቀጥላል!!››  (የጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን አጥቢያ ወጣቶች)
  • ‹‹ሊቀ ካህናት›› ጌታቸው ዶኒ በመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክ የገዳማት አስተዳደር መምሪያ ሐላፊ ሆነው መሾማቸው እየተነገረ ነው፤ የጅጅጋን እና የአዲስ አበባ ሀገረ ስብት ሥራ አስኪያጆችን ለማስነሣት የአድማ ፊርማና ምክክር እየተካሄደ  ነው
(ደጀ ሰላም፤ ጁን 5/2011)፦ እሑድ ግንቦት 29 ቀን 2003 ዓ.ም፤ ከረፋዱ 5፡00 ሆኗል፡፡ ጠዋት በማኅደረ ስብሐት ልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን በሥርዐተ ተክሊል ጋብቻውን የፈጸመው ዘማሪ ፈቃዱ አማረ ወደ ሠርጉ የጠራቸው ታዳሚዎች ወደሚጠባበቁበት የደብረ አሚን ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን አዳራሽ እያመ ነው፡፡ በደብሩ አዳራሽ ቀደም ብለው የተገኙት ዘማሪዎች (ዳግማዊ ደርቤ፣ አሸናፊ አበበ፣ ታምራት እና የትምወርቅ) ማቀንቀናቸውን ቀጥለዋል፡፡

ሞያ በልብ ያሉት የደብሩ ዲያቆናት፣ የሰንበት ት/ቤት አባላት እና በቀናዒነታቸው የታወቁት የአጥቢያው ወጣቶች ደግሞ ስለ መርሐ ግብሩ ዝርዝር እና በመርሐ ግብሩ ላይ ስለሚያገለግሉ ሰባክያን እና ዘማርያን ማንነት አስቀድመው ከሙሽራው ጋራ በተነጋገሩት መሠረት ቦታ ቦታቸውን ይዘው ገቢውንና ወጪውን እየቃኙ አካባቢውን በንቃት እየተቆጣጠሩ ነው፡፡ አስቀድሞ ከሙሽራው ጋራ በተደረገው ንግግር ወጣቶቹ፣ ‹‹በቅዱሳን ላይ አፋቸውን አላቅቀዋል፤ በጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ላይ የስድብ ቃል ተናግረዋል፤ በሃይማኖታቸው ሕጸጽ አለባቸው፤ የፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ-ኑፋቄ መልእክተኞች ናቸው›› ያሏቸውን ሰባክያን እና ዘማርያን ስም በመዘርዘር እግራቸው ሰበካውን እንዳይረግጥ እንዲያስጠነቅቃቸው፣ ይህ ካልሆነ ግን የከፋ ርምጃ እንደሚወስዱባቸው አስታውቀዋል፤ በዚህም መሠረት መልእክቱ በተለያየ መንገድ እንደደረሳቸው ተረጋግጧል፡፡ ወጣቶቹ ይህንኑ ስጋታቸውንና ማስጠንቀቂያቸውን ለደብሩ አስተዳደርና ለአቅራቢው የፖሊስ ማዘዣ ጣቢያ በጻፉት ደብዳቤ በማሳወቃቸውም ከ40 ያላነሱ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኀይሎች በደብሩ ዙሪያ ተገኝተዋል፡፡

ከየአብያተ ክርስቲያኑ ዐውደ ምሕረት ቢወገዱም እንደ ድንኳን ሰባሪ ሳይጠሩ በየሠርጉ አዳራሽ እየገቡ በማወክ የኦርቶዶክሳውያንን ልብ ማቁሰልን ሥራዬ ብለው የተያያዙት ዘማሪ እና ሰባኪዎቹ ግን የወጣቶቹ የቅድሚያ ማስጠንቀቂያ ሳይገታቸው ከመናፍቃኑ ጋራ አብረው ተባብረው ጽርፈት ወደሚናገሩባቸው ጻድቅ አጥቢያ ያለኀፍረት ለመምጣት ደፈሩ፡፡

‹‹ደጅሽ ላይ ቆሜ እጠራሻለሁ›› በተሰኘውና በሌሎች አምስት የአልበም ሥራዎቹ የሚታወቀውን ሙሽራውን ዘማሪ ፈቃዱ አማረን የያዘው መኪና ከደብሩ ቅጽር ሲደርስ እግራቸው ሰበካውን እንዳይረግጥ ማስጠንቀቂያ ከተላለፈባቸው ሕገ ወጦች አንዱ የሆነው እስጢፋኖስ ሣህሌ(በቅጽል ስሙ ቄሴበመኪናው ውስጥ እንዳለ በወጣቶቹ እልምት ውስጥ ገባ፡፡ ለሙሽራው ሁለተኛ ሚዜ እንደ ነበር ተነግሯል፡፡

ከመኪናው እንዲወርድ በወጣቶች የታዘዘው እስጢፋኖስ ሣህሌ ከመኪናው እንደወረደ የተቀበለው ሰማይ ምድሩን የሚያዞር ጥፊ ነበር፡፡ ለሙሽራው ሁለተኛ ሚዜ በመሆኑ አስተያየት እንዲደረግለት የጠየቁ ምእመናን ቢኖሩም ‹‹የእርሱ ሚዜነት ከተክልዬ ክብር አይበልጥም፤ ሲሳሳት አታርሙትም!!›› ነበር የወጣቶቹ መልስ፡፡ እስጢፋኖስ እየተገፈተረ ከቅጽሩ እንዲወጣ ተደረገ፡፡

ይህ ርምጃ በሚወሰድበት ቅጽበት የሕገ ወጥ ቡድኑ ‹‹ሶፍትዌር›› እንደሆኑ  ከሚነገርላቸው ግለሰቦች አንዱ የሆነው አሸናፊ ገብረ ማርያም ወደ ቅጽሩ ገብቶ በመሳለም ላይ ነበር፤ የሚከታተሉት ወጣቶችም በመጠጋት ‹‹አሸናፊ፣ የሰደብሃቸውን ተክልዬን ከተሳለምህ ይበቃሃል፤ ከዚህ በኋላ ቀጥ ብለህ ውጣ›› ይሉታል፤ አሸናፊ ግን በእምቢታ ያንገራግራል፤ ከወሬ ይልቅ ተግባራዊነትን መርሃቸው ካደረጉት ወጣቶቹ አንዱ ቀሲስ አሸናፊ በሱሪ ኪሱ የያዘውን/በአባ ሰረቀ አነጋገር የወተፈውን/ መስቀል፣ ‹‹ማነው ይህን መስቀል ለአንተ የሰጠህ?›› በሚል ላጥ አድርገው ይነጥቁታል፡፡ ወዲያው ሌላው ወጣት ቡጢ ይመታዋል፤ የወጣቶቹን ማምረር ለመረዳት እልኩ ያልረዳው አሸናፊም ‹‹እናትህ. . . ›› በማለት የመታውን ወጣት ይሳደባል፤ የዐይን እማኞች እንደተናገሩት እንኳንስ ከ‹‹ቀሲስ›› ከሌላው በማይጠበቀው በዚህ ስድቡ የወጣቶቹን ቁጣ ያባባሰው አሸናፊ ፋታ በማይሰጠው የወጣቶቹ ጥቃት እየተመታ በገላጋዮች ብርታት ክፉኛ ከመጎዳት ተርፎ ከስፍራው ተሸኝቷል፡፡ እርሱ እየተሸኘ ወደ ቅጽሩ በመግባት ላይ የነበራችው ምርትነሽ አንድ ጥፊ አርፎባት በመጣችበት አኳኋን ስትመለስ እያለቀሰች ነበር፡፡

ወጣቶቹ በመቀጠል ወደ አዳራሹ አመሩ፤ ቀደም ብሎ ወደ አዳራሹ ዘልቀው ለአፍታም ቢሆን ድምፅ ማጉያ ለመጨበጥ ዕድል ካገኙት ውስጥ የትምወርቅ እና ቅድስት ምትኩ ከአዳራሽ ታንቀው ከወጡ በኋላ የወጣቶቹን ጉሽሚያና ርግጫ እየቀመሱና እያለቃቀሱ በአስቸኳይ ከአካባቢው እንዲርቁ ተደረጉ፡፡

ዳግማዊ ደርቤ ‹‹የቦኤዝን እርሻ አልቃርምም እኔ. . .›› እያለ በአዳራሹ በማዜም ላይ ነበር፡፡ የወጣቶቹን ሁኔታ አስቀድመው የተመለከቱ ጓደኞቹ ማዜሙን እንዲያቆም መክረውት ነበር፤አንድ ወጣት ትከሻውን መታ አድርጎ ካስቆመው በኋላ እየገፋ ወደ ውጭ እንዳስወጣው የበሩን ግራና ቀኝ ይዘው የቆሙ በረኞች የቡጢ ናዳ ይቀበለዋል፡፡ አንድ የዐይን እማኝ እንደ ተናገሩት፣ ዳግማዊ ከቅጽሩ የወጣው ወጣቶች ትክሻ ነበር፡፡

ወጣቶቹ በግልጽ የሚያውቋቸውን ሕገ ወጦች ካባረሩ በኋላ ማንነታቸውን የማይለዩዋቸው ሌሎች መኖራቸውን ለመለየት በጠቋሚ አሰሳ አደረጉ፤ እንደ ዐይን ምስክሮቹ ማብራሪያ በነደደ ቁጣ የታጀበችው ይህች የወጣቶቹ አሰሳ ቀና የሚባሉትንና በሠርጉ ላይ ለታደሙት ሌሎች አገልጋዮች ሳይቀር አርዕድ አንቀጥቅጥ የሆነች ቅጽበት ነበረች፤ ራሳቸውን በየሰዉ ጀርባ ሲሸሽጉ የተስተዋሉም ነበሩ፡፡ በአሰሳው የሕገ ወጦቹን ዘማርያን እና ሰባክያን ሥራ በማሳተምና በማከፋፈል ተሳትፎ አላቸው የተባሉት የአብ፣ የቢታንያ፣ የቬሮኒካ እና የአንጾኪያ መዝሙር ቤት ባለቤቶች ተለይተው እንዲወጡ ተደርገዋል ተብሏል፡፡ ከሕገ ወጦቹ ጋራ በመሞዳሞድ ወላዋይ አቋም የሚታይባቸው አገልጋዮችም በወጣቶቹ ማሳሰቢያ /ቢጫ ካርድ/ ተሰጥቷቸዋል - ምንጮቹ ማሳሰቢያ የተሰጣቸውን አገልጋዮች ስም ከመጥቀስ ተቆጥበዋል፡፡ በአዳራሹ የአሸናፊን ድርሰት ስታዜም የነበረች አንዲት ዘማሪም ምርጫዋን አስተካክላ ተገቢውን መዝሙር እንድትዘምር አድርገዋታል፡፡

ለሙሽራው ቅርብ የሆኑ የዜናው ምንጮች ዘማሪ አማረ ፈቃዱ ሕገ ወጦቹን ዘማርያን እና ሰባክያንን አለመጥራቱን፣ ቢመጡም መድረክ እንዳይሰጣቸው አስተባባሪዎቹን አዝዞ እንደ ነበር አስረድተዋል፡፡ በአንጻሩ ወጣቶቹ የቀና ሃይማኖታዊ አቅዋም እንዳላቸው ያመኑባቸውን አገልጋዮች በታላቅ አክብሮት እየተቀበሉ ሲያስተናግዱ ታይተዋል፤ ከሕገ ወጦቹ አገልጋይ ነን ባዮች ይልቅ ነጻ አገልግሎት ለመስጠት ለብሰው ከተዘጋጁት የሰንበት ት/ቤቱ ወጣት ክፍል አባላት በኵረ ትጉሃን ፈንታ ገላው መርሐ ግብሩን በመምራት፣ መ/ር ዘመድኩን በቀለ እና ዲያቆን ታዴዎስ ግርማ መርሐ ግብሩን በማስተባበር፣ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት የዕለቱን ትምህርት በመስጠት፣ ዘማርያኑ ዲያቆን ልዑል ሰገድ፣ ዲያቆን እንግዳ ወርቅ፣ አረጋዊ፣ ለሰባክያን ጥምረቱ ቀጣይ የገንዘብ ርዳታ በማስተባበር እየረዳች የምትገኘው ዘማሪት ፋንቱ ወልዴ እንዲሁም አዲስ ለማ በመዘመር ሲያገለግሉ ውለዋል፡፡ መምህር ዳንኤል ክብረት ‹‹ወሳኙ ሃይማኖት ነው›› በሚል ርእስ በሰጡት በዚሁ ትምህርት ‹‹ሃይማኖት የሌለው ሰው በሰማይም በምድርም መቅሠፍት አያጣውም›› ማለታቸው ተዘግቧል፡፡

በዙሪያው እና በቅጽሩ ክዋኔውን በአንክሮ እና በድንጋጤ ሲታዘቡ የነበሩ ምእመናን፣ ‹‹ደግ አደረጉ! እነርሱስ ቢሆን ማን ኑ አላቸው? ደብሩኮ ተክለ ሃይማኖት ነው፤ ከጥንት ጀምሮ ይታወቃል፤ እየተነገራቸው/እያወቁ መምጣታቸው ድፍረት ነው፤ ቃለ እግዚአብሔሩን እንደሆን አይመሩበትም፤ አሁን እንኳ ዱላ ነው የሚገባቸው!! ድሮም የበላዮቹ ሳይሆኑ የምእመኑ ብርታት ነው ቤተ ክርስቲያንን የጠበቃት…›› ሲሉ መደመጣቸው ተዘግቧል፡፡ ሌሎች የሰንበት ት/ቤቱ አባላት ደግሞ ቦታው የለመደ ስለ መሆኑ ተመሳሳይ ትውስታቸውን አካፍለዋል።

በ1986 ዓ.ም ክረምት ወራት አሁን በሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ባለሥልጣን ከሆኑ ግለሰቦች አንዱ በወቅቱ በመላው የአዲስ አበባ ሰንበት ት/ቤቶች ሲሰጥ የነበረውን የፀረ-ተሐድሶ ኑፋቄ ኮርስ ለማስቆም ይነሣሣሉ፤ በዚህ ጊዜ የአካባቢው ወጣቶች እኚህ ባለሥልጣን አይደለም በጻድቁ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን መገኘት ከፒያሳ በታች የመውረዳቸው ዜና ቢሰማ ልክ እንደሚያገቧቸው ስላስጠነቀቋቸው ጥቂት ለማይባል ጊዜ ተሸማቅቀው ይኖሩ እንደነበር ተመልክቷል፡፡ በዚሁ ዓመት ጾመ ሁዳዴ ከመግባቱ በፊት ሠርጋቸውን በአጥቢያው አዳራሽ ያደረጉ ሌላ ስም ያወጡ አገልጋይም የጋበዙት መምህር የማይሆን ስለነበር በወጣቶች ማስጠንቀቂያ በሌላ ተተክተዋል፡፡

‹‹የቤተ ክርስቲያን አባቶች ዝም በማለታቸው የዛሬውን ርምጃ ለመውሰድ ተገደናል፤›› ያሉት የአጥቢያው ወጣቶች ‹‹የተክለ ሃይማኖት ድል በዮሴፍም ይደገማል፤›› በማለት እነበጋሻው በየሳምንቱ የሚፈነጩበትን የደብረ ናዝሬት ቅዱስ ዮሴፍ ቤተ ክርስቲያን ዐውደ ምሕረት ከሕገ ወጦች በማጽዳት ርምጃቸውን እንደሚቀጥሉ ዝተዋል፡፡ በሌላ በኩል መንፈሳዊ ቅንዐት የተመላበት የወጣቶቹ የማጽዳት ርምጃ የራሱ ምልከታዎች እንዳሉት ስለ ድርጊቱ የወጡ አስተያየቶች ይጠቁማሉ፡፡ ከእኒህም መካከል፣ ‹‹የቤተ ክርስቲያን አባቶች በተቆርቋሪ ወገኖች የሚሰጣቸውን መረጃ መዝነው ተገቢውን አፋጣኝ ርምጃ ያለመውሰዳቸው ‹እግርን መጎተት› አልፎ አልፎም ዳተኝነት የወለደው ነው››፤ ‹‹ስለ ወቅታዊው የቤተ ክርስቲያን ችግር የሚተላለፈው መልእክት የጥቂቶች መሆኑ አብቅቶ ምእመኑን የተዋሐደው መሆኑንና ምእመኑ የተግባር መመሪያው ማድረጉን የሚያረጋግጥ ነው››፤ ‹‹አገልጋዮች ስለሚዘምሩበት እና ስለሚያስተምሩበት ጉዳይ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ያሳሰበ ነው፤›› የሚሉት ይገኙባቸዋል፡፡

የሐዋሳ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በ‹‹ተስፋ ኪዳነ ምሕረት›› አመራሮች ላይ የእስር ቅጣት ወሰነባቸው
(ደጀ ሰላም፤ ሜይ 4/2011)፦ የሐዋሳ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በሚያዝያ ወር ውስጥ በደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ባስነሡት ብጥብጥ በንጹሐን ምእመናን ላይ ከፍተኛ የድብደባ ወንጀል ፈጽመዋል ባላቸው አራት የ‹‹ተስፋ ኪዳነ ምሕረት›› ማኅበር አመራር በሆኑ ተከሳሾች ላይ የተለያዩ የቅጣት ውሳኔዎችን አስተላልፏል፡፡ ፍርድ ቤቱ ሐሙስ፣ ግንቦት 27 ቀን 2003 ዓ.ም በዋለው ችሎት ገዛኸኝ አበራ እና አየነው የተባሉት ግለሰቦች በ8 ዓመት፣ ተስፋዬ በ5 ዓመትና ጌታሁን የተባሉት ደግሞ በ3 ዓመት እስራት እንዲቀጡ ወስኖባቸዋል፡፡

ውሳኔው በተላለፈበት ዕለት ምሽት የእኒሁ ወንጀለኞች ጥቂት ደጋፊዎች በገዳሙ ዐውደ ምሕረት ላይ በመውጣት በድምጽ ማጉያ ‹‹ወንድሞቻችን ተፈረደባቸው፤ ታሰሩ፤›› እያሉ የከተማውን ደጋግ ምእመናንን እና የማኅበረ ቅዱሳንን ስም እየጠሩ ሲወነጅሉ እንደነበር ተገልጧል፡፡ እኒሁ ግለሰቦች በሊቀ ጳጳሱ ብፁዕ አቡነ ገብርኤል ተመርጠውና በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ተመድበው የሄዱትን አዲሱ ሥራ አስኪያጅ ወደ ቢሯቸው እንዳይገቡ ለመከላከል ሞክረው እንደነበር ታውቋል፡፡ ይሁንና በፖሊስ ኀይል ከአካባቢው እንዲርቁ ከተደረገ በኋላ ሥራ አስኪያጁ ሥራ ለመጀመር መቻላቸው ተመልክቷል፡፡

በቅዱስ ሲኖዶሱ ውሳኔ አላግባብ ከተሰጣቸው ሥልጣን እንዲወገዱ የተደረጉት ‹‹ሊቀ ካህናት›› ጌታቸው ዶኒ በተሰራጨው ቪ.ሲ.ዲ ስሜ ጠፍቷል ያሉበትን ክስ በዚያው በሐዋሳ ከተማ ሆነው እየተከታተሉ ሲሆን ግንቦት 27 ቀን 2003 ዓ.ም በመንበረ ፓትርያሪክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የገዳማት አስተዳደር መምሪያ ምክትል ሐላፊ ሆነው መሾማቸው ተነግሯል፡፡
ምንጭ ደጀ ሰላም